Job 16

ኢዮብ

1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤

2“ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ሰምቻለሁ፤
እናንተ ሁላችሁ የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ።
3ይህ ከንቱ ንግግር አያልቅምን?
ትለፈልፍ ዘንድ የሚገፋፋህ ምንድን ነው?
4እናንተ በእኔ ስፍራ ብትሆኑ ኖሮ፣
እኔም እንደ እናንተ መናገር እችል ነበር፤
ቃላት አሳክቼ በመናገር፣
በእናንተ ላይ ራሴን መነቅነቅ በቻልሁ ነበር።
5ይልቁንም አንደበቴ ባበረታታችሁ፣
የከንፈሬም ማጽናናት ባሳረፋችሁ ነበር።

6“ብናገር ሕመሜ አይሻለኝም፤
ዝም ብልም አይተወኝም።
7እግዚአብሔር ሆይ አሁንስ አድክመኸኛል፤
ወገኖቼንም ሁሉ አጥፍተሃል።
8ጭምትርትር ያደረግኸኝ ምስክር ሆኖብኛል፣
ዐጥንቴን ያወጣው ክሳቴም ያጋልጠኛል።
9በቍጣው ሰነጠቀኝ፤ በጥላቻው አስጨነቀኝ፣
ጥርሱን ነከሰብኝ፤
ባላጋራዬ ክፉ ዐይኑን ተከለብኝ።
10ሰዎች በፌዝ አፋቸውን ከፈቱብኝ፤
በንቀት ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤
በአንድነትም በላዬ ተሰበሰቡ።
11እግዚአብሔር ለክፉዎች አሳልፎ ሰጠኝ፤
በጠማሞችም እጅ ጣለኝ።
12በሰላም እኖር ነበር፤ እርሱ ግን ሰባበረኝ፤
ዐንገቴን ይዞ አደቀቀኝ፤
ማነጣጠሪያ ዒላማው አደረገኝ፤
13የእርሱ ቀስተኞች ከበቡኝ፤
ያለ ርኅራኄ ኵላሊቴን ይበጣጥሳል፤
ሐሞቴን መሬት ላይ ያፈስሳል።
14ደጋግሞ ይቀጠቅጠኛል፤
እንደ ጦረኛም ተንደርድሮ ይመጣብኛል።

15“በቈዳዬ ላይ ማቅ ሰፍቻለሁ፤
ክብሬን በዐፈር ውስጥ ቀብሬአለሁ።
16ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀልቷል፤
ጨለማም በዐይኖቼ ቆብ ላይ ዐርፏል፤
17ነገር ግን በእጄ ዐመፅ አይገኝም፤
ጸሎቴም ንጹሕ ነው።

18“ምድር ሆይ፤ ደሜን አትሸፍኚ፤
ጩኸቴም ማረፊያ አያግኝ!
19አሁን እንኳ ምስክሬ በሰማይ አለ፤
ጠበቃዬም በላይ በአርያም ይገኛል።
20ወዳጆቼ በንቀት ቢመለከቱኝም፣
ወይም ወዳጆቼ አማላጅ ቢሆኑልኝም

ዐይኔ ወደ እግዚአብሔር ያነባል።
21ሰው ለወዳጁ እንደሚማልድ፣
በእግዚአብሔር ፊት የሚማልድ ሰው ምነው በተገኘ!

22“ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣
ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።
Copyright information for AmhNASV